አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት 20/2015 በአህጉራዊ የቁርዓን ውድድር ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመለየት በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ዓመታዊው የቁርዓን ውድድር ተጠናቀቀ ፡፡
በውድድሩ ከሶማሌ ክልል የመጣችው ሰፍያ ሸህ አህመድ እና የአዲስ አበባው አባስ መህዲ አሸናፊ ሆነዋል።
ውድድሩን ያዘጋጀው ዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበር ከሞሮኮው ንጉስ መሃመድ ስድስተኛ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ነው፡፡

በአህጉራዊው የቁርዓን ውድድሩ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ አባላትን ለመምረጥ በተዘጋጀው በዚሁ ውድድር 50 ኢትዮጵያዊያን ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ መሆናቸውን በዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበር ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርዓንና የአዛን ውድድር ዋና ኃላፊ ዶክተር ኑረዲን ቃሲም ተናግረዋል፡፡
ውድድሩ ሀገራችንን የሚያስተዋውቅ መሆኑንም ዶክተር ኑረዲን አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን ከሌላው ዓለም ሕዝቦች ጋር የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉ እድል እንደሚፈጥርም እንዲሁ፡፡
አሸናፊዋ በአፍሪካ 32 አገራት የሚሳተፉበትና ሞሮኮ በሚካሄደው የቁርዓን ውድድር ላይ እንደምትሳተፍ ተገልጿል፡፡
የቁርዓን ውድድሩ የኃይማኖትን ዕውቀት ከማሳደጉም በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኑዝሓ አላዊ ይህን አይነት ዝግጅቶች የሞሮኮና ኢትዮጵያን ግንኙነቶች የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያና ሞሮኮ የሚጋሩዋቸው በርካታ ትውፊቶች ያላቸው ሀገራት ናቸው ያሉት አምባሳደሯ ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዘበዋል።
በዝግጅቱ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ አምባሳደሮችና የሞሮኮ ልኡካን ቡድን አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።